ሠላም ጤና ይስጥልኝ ክቡራን አንባቢያን ፤ ከዚህ መካነ-ድር (ድረ ገፅ) ላይ የምትወስዱትን ማንኛውንም ፅሑፍም ይሁን ምስሎች ለአዘጋጆቹ እና ለፀሐፊዎቹ ክብር ሲባል በምትጠቀሙበት ቦታ ሁሉ ምንጩን ትጠቅሱልን ዘንድ በትህትና እናሳስባለን ፡፡

Wednesday, April 3, 2024

የዝቋላው ሀዘን - ይፍቱኝ

 ሰላም ወዳጆች እንዴት ከረማችሁ?

ፌስቡክ መጠቀም ማቆም እረፍት አይደል እንዴ?
ከዚህ በኋላም በተጠናከረ ሁኔታ ከፌስቡክ ዓለም ለመውጣት ዝግጅት ላይ ነኝ።
ሃሃሃሃ
የምን ዝግጅት ?....... ወጥቻለሁ።
ደህና የጨመርኩትን ኪሎማ አልቀንስም...

ቁም ነገር ግን ለምን አትሉም?

ከልብ ስሙን.... ፌስ ቡክ ከገባሁ አርባ ቀናት አለፉኝ። ከዝቋላ አባቶች ግድያ ጀምሮ...

ይኸው #የዝቋላ አባቶችን በነፈስ በላው ስርዓት ካጣን እና አርባ ቀናቸውን ካወጣን ቀናት ተቆጠሩ። እኔም ቤተሰቤም አባ ኪዳነ ማርያም (የገዳሙ ጸሐፊ የነበሩት) የእኔ ደግ አባት በረከታቻው ይደርብኝና ካጣኋቸው ሰነበትኩ ፤ ሰነበትን። እኔም ዜና እልፈታቸውን ከሰማሁ በኋላ እኔም እኔ አይደለሁም። ብዙ ነገሬ ወድቆ ተሰባብሯል።
ኡፍፍፍ ህይወት እንደ ቀልድ የምታልፍበት ሀገር ላይ ሆኖ ተስፈኛ መሆን እንዴት የሚያደክም መሰላችሁ። ያደክማል። ላለፉት አርባ ቀናት ከአንድ ወይም ሁለት ቀን ውጪ ከቤቴ አልወጣሁም።
ምን ለማየት ምን ለማግኘት ልውጣ?

ወዳጆቼ አሁን ላይ በመንፈሳዊም ሆነ ዓለማዊ ትምህርት የትኛውም ከፍታ ላይ ብትገኙ የእናንተን የመኖርና የአለመኖር ሁኔታ በደቂቃ ውስጥ የሚወስኑት . . . . . . . ሁነዋል ሀገራችንን የሚመሯት ። ይሄ እንዴት አያስከፋ አያሳዝን። ሀገሬ ማልቀስ ከጀመረችና ሀዘኗ ከበረታ ከጨለመች ሰነበተች።
ምን ብርሃን ምን ተስፋ ይታየኝ ዝም ከማለት ውጪ...
ጥቅመኛ ካልሆነ አሁን ላይ በሀገሩ ተስፋ የሚታየው አለ ይሆን?

Thursday, December 22, 2022

ደብረ ዓባይ አቡነ ሳሙኤል ገዳም - ታኅሳስ 12

         አባታችን አቡነ ሳሙኤል ደብረ ዓባይንና ዋልድባን ያቀኑ ታላቅ ጻድቅ ሲሆኑ የተወለዱት ቦታም በትግራይ ክፍለ ሀገር በርዕሰ ገዳማት ወአድባራት አክሱም ጽዮን በ 1298 ዓ.ም ከአክሱም ባላባቶች እና ካህናት እንዲሁም የአክሱም ጽዮን ገበዝ ከሚሆን ከጌዴዎን ዘር ከእስጢፋኖስና ከዓመተ ማርያም ተወለዱ።

በተወለዱም በ7 ዓመታቸው ወደ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገብተው በአጭር ጊዜ ትምህርታቸውን አጠናቀው በ 1314 ዓ.ም መንነው ወደ ደብረ በንኮል ገዳም ገብተው በአቡነ መድኃኒነ እግዚእ እጅ መነኮሱ። በደብረ በንኮል 3 ዓመት በርድና 9 ዓመት በምንኩስና ጠቅላላው 12 ዓመት አገለገሉ። ከዚያ በኋላ ከዚያ ወጥተው ወደ በጌምድር በመሄድ በወይና ፣ በመንዳባ ፣ በዞዝ ፣ በአዘዞና በአብጠራ ወዘተ እየተዘዋወሩ በየዋሻው ሱባዔ እየገቡ በጾም በጸሎት በስግደት በአርምሞ በተለያየ ገድል 19 ዓመት ከተቀመጡ በኋላ ወደ ሽሬ አውራጃ ተመልሰው በየቦታው እየተዘዋወሩ የገበሬዎችን ዘር እየባረኩ ሕሙማንን እየፈወሱ ሙታንን እያስነሱ ትምህርተ ወንጌልን እየሰበኩ ብዙ ሕዝብን ካሳመኑ በኋላ በ1353 ዓ.ም ወደ ደብረ ዓባይ ገቡ። ገብተውም የቦታውን ጽሙናና የቦታውን ስፋት አይተው በጣም ተደስተው ሱባዔ ቢገቡ ብዙ ተአምራት ተደርጎላቸዋል። 
ከተአምራቶቹም ጥቂቶቹ ውዳሴ ማርያምን እና ቅዳሴ ማርያምን ደግመው ውሃውን ቢባርኩት ኅብስት ሆኖላቸው አርድእቶቻቸውን መግበዋል።

እስከ ዛሬ ድረስ ገዳሙ የሚገለገልበት "ማይ ምንጭ" የሚባለውን ውሃ ባርከው አፍልቀዋል። ቅዱስ ሚካኤል ወደ ሰማይ አሳርጎ የሰማይ መኖሪያቸውን አሳይቷቸዋል። እራሱ ጌታችንም ከንጽሕት እናቱና ከአእላፍ መላእክት ጋር ሰማያዊ የመድኃኔዓለም ታቦትን ይዞ መጥቶ ሰጥቷቸው ይህች ቦታ ቦታህና መካነ ርስትህ ናት ብሎ ቃል በቃል ተነጋግሯቸው ዐርጓል።
በተነጋገሩበት ቦታ የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ተሰርቶበት እስከ ዛሬ ድረስ ይገኛል።

Wednesday, May 25, 2022

ኦርቶዶክሳዊነት እና የሰይጣን መንግስት

 ላለፉት ዓመታት ማህበራዊ ገጾችን በተለይ ፌስቡክን ለምፈልገው ዓላማና ግብ ስጠቀምበት ነበር። ይሁንና ከጥቂት ዓመታት ጀምሮ ግን "እያስጠላኝ" በመምጣቱ ምክንያት እንደከዚህ ቀደሙ እይታዬን ፣ ፍላጎቴን ፣ ልምዴን ለማካፈል የነበረኝ ተነሳሽነት እየቀነሰ መጥቷል። በዚህም የፌስቡክ ጥቅም ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ምን እንደሆነ እየጠፋኝ እና እየዘነጋሁት መምጣት ጀምሯል።

ይኼ ሁኔታ ልክ ይሁን ልክ አይሁን አሁን ላይ ማሰብ ባልፈልግም እንደዛሬው አይነት ጉዳይ ሲገጥመኝ ግን እንደሁኔታዎች እራሴን መፈተሽ እንዳለብኝ ተሰምቶኛል።

ከአንድ ወዳጄ ጋ ሻይ ቡና እያልን ስለሀገራችን አኹናዊ ሁኔታ ስንጫወት በመሐል ኦርቶዶክሳዊነት እና ብልጽግና ስለሚባለው  ኮተት መዋቅር አንስተን መጫወት ጀመርን። ጥሩ ጥሩ ሃሳቦችን አንሸራሸርን። አድምቀን አድምተን ተወያየን።

በመሐል 

" ብስሬ የመምህር ፋንታሁን ዋቄን አዲሱን መጽሐፍ ገዝተህ አንብበው ፤ ምን ያህል ኦርቶዶክሳዊነትን ለማጥፋት እየሰሩ እንዳለ ግንዛቤ ይሰጣል " አለኝ።

ለጥሩ ውይይት ትክክለኛ ግብዣ ብዬ መጽሐፉን ማንበቤን ልነግረው አልኩና ስለመጽሐፉ የተሰማውን በዝርዝር እንዲያወራ ስለፈለኩ ተውኩት። 

መጽሐፉ፦

Wednesday, July 11, 2018

ማነው ገንጣዩ?

          የዚህ ፅሑፍ መነሻ አንድ የማከብረው ወዳጄ 'ትግራይ' ብትገነጠል ምንም አናጣም... የትግራይ ሠው ማለት እንደዚህ ነው... ትግሬ ማለት እንደዚህ ነው... እያለ የወረደ እና የሚያበሳጭ ፍሬአልባ ፅሑፍ ፅፎ ማየቴ ነው። የገረመኝ 'ተደምሬያለሁ' የሚል ቲሸርት ለብሶ ፈገግ ኮራ ብሎ የተነሳውን ፎቶ ጨምሮበታል። እርግጥ ነው በሒሳብ ስሌት 'መደመር' ገደብ የለውም። ከማንም ጋር ከምንም ጋር መደማመር ይቻላል። ውጤቱም እንደተደማሪው ዓይነት ፣ ይዘት ይወሰናል። እንግዲህ ከማን ጋር እንደተደመረ እሱ ይወቀው።
ሠሞነኛው ሙቀት መሠለኝ አሁን አሁን በተጠናከረ ሁኔታ ስለ ትግሬ እና ትግራይ መልካም ነገር እየተነገረ አይደለም። ምንም እንኳን ጥቂቶች በተቃውሞ ቢሟገቱም!

    "ስታጠፋ ምላስ እንጂ አቋም አያስፈልግም" እንደሚባለው አንዳንዶች ጥላቻን ለማስፋፋት ፈለገው ፣ አንዳንዶች በአለማወቅ ፣ በአስተሳሰብ ጥበት ፣ ሌሎች 'ትገንጠል አታስፈልግም' በማለታቸው የሚበላ ትርፍራፊ እንጀራ በማግኘት  ይኖራሉ። ሁሉም ግን አይረቡም። 
እንደዚህ የወረደ ፣ ታጥቦ የማይጸዳ ፣ የመነቸከ ስብዕና ተሸክመው የሚኖሩ እነሱንም በመደገፍም በማራገብም ከጎናቸው የሆኑ ሁሉ 'ትግራይ' ሳትሆን እራሳችሁ ከህዝቡ ከማህበረሰቡ ብትገነጠሉ ለኢትዮጵያ ትልቅ አስተዋጽዖ እና ዘላቂ ጥቅም ነው። ችግሩ ተገንጠሉም ብትባሉም ይህን የሚያስደርግ ወኔም ድፍረትም የሌላችሁ መሆኑ ነው። እንደመርዘኛ እባብ ተሸሽጎ የጥላቻ የመከፋፈል ቃላትን መወርወር ካልሆነ።

                 ባለፉት 27 ዓመታት መገነጣጠል መከፋፈል ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል። ያለንን ደም መጦ ጨርሶ በአጥንታችን አስቀርቶ ተፈታትኖናል ፤ ጥንካሬያችንን ሰብሮ ህብረታችንን በትኖ ፍቅራችንን አጠልሽቶ ክብር አልባ ሀገር አልባ ወገን አልባ ዕምነት አልባ ሊያደርገን ሞክሯል።

Saturday, April 14, 2018

የዋልድባዎቹ መነኮሳት

              በሽብርተኝነት ተከሰው ከሁለት ዓመት በላይ ታስረውን እጅግ የበዛ መከራና ስቃይ ሲቀበሉ የነበሩት ሁለት አበው መነኮሳት ማለትም አባ ገብረኢየሱስ ኪዳነማርያም እና አባ ገብረስላሴ ወልደሃይማኖት ዛሬ ከእስር ተፈተዋል፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ በፊት የአባቶቻችንን መፈታት ደጋግሞ ሲጠይቅ ለነበረው የኢትየጵያ ህዝብ የአባቶቹ መፈታት እንደመልካም ዜና እንደሚያስበው አምናለሁ፡፡ ምክያቱም በወቅቱ አባቶች ይፈቱ በሚለው ድምፅ ውስጥ ሙስሊም ማህበረሰቡም ተሳታፊ የሆነባቸው ወቅቶች ስለነበሩ፡፡

ከፍተኛው ፍርድ ቤት በቀን 03 -08 -2010 ዓ.ም የአንድ መቶ አስራ አራት (114) እስረኞችን ክስ አቋርጠናል ብለው ሲገልጹ የአባቶቻችንን ስም ተካቶ የነበረ ሲሆን በዛሬውም ዕለት በቀን አርብ 05 -08 -2010 ዓ.ም ከቀኑ 5 ሰዓት ላይ ፍርድ ቤቱ የእስረኛ መፍቻ ደብዳቤ ለቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በመፃፉ ያለወንጀላቸው ሁለት ዓመት በላይ የታሰሩት እስር አባቶቻችን ሊፈቱ ችለዋል፡፡ ለዚህም የብስራት እይታ ድረገፅ አዘጋጆች የተሠማንን ደስታ መግለፅ እፈልጋለሁ፡፡ ይችን ቀን በመናፈቅም ስንጠብቃት ነበር፡፡

አባቶቻችን ወደበዓታቸው ተመልሰው ለእናት ሀገራችን እንደሚፀልዩ እንደሚያለቅሱ እናምናለን፡፡ ለዚህም የእግዚአብሔር ፈቃድ ይሆን ዘንድ ምኞታችን ነው፡፡

ፅሑፌን ከማብቃቴ በፊት አባቶቻችን ከእስር ከተፈቱ በኋላ ለVOA ሬዲዮ የተናገሩትን ታሪክ ተሻጋሪ ንግግር ወደፅሑፍ ቀይሬ እንድታነቡት እጋብዛለሁ፡፡ መልካም የፋሲካ በዓል እንዲሁም መልካም የዳግማ ትንሳይ በዓል ይሁንላችሁ፡፡